AleHig Law Office is a premier legal office specializing in a wide range of legal services in Ethiopia, Addis Ababa, including government engagement, corporate law, investment, commercial law, business law, property disputes, family law, succession, and civil law cases

FOLLOW US ON:

Get in touch!

Addis Ababa, Ethiopia

የጥብቅና ፈቃድ እና የጠበቆች ሙያዊ ግዴታ

  • Home
  • Amharic Laws
  • የጥብቅና ፈቃድ እና የጠበቆች ሙያዊ ግዴታ

ሰዎች በእለት ተዕለት የማህበራዊ ህይወት መስተጋብር የሚገጥሟቸውን አለመግባባቶች በፍርድ ቤት ወይም በሌሎች አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶች ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሂደትም የህግ ባለሞያዎችን እገዛ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ በጠበቆች ተወክለው ክርክራቸውን ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ፅሁፍ ከፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ 1249/2013 አንፃር የጠበቃን ምንነት፣ የጥብቅና ፈቃድ ለማግኘት ሊሟሉ የሚገባቸውን መስፈርቶች እንዲሁም ጠበቆች ያለባቸውን ሀላፊነት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የጠበቃ ምንነት
በፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1249/2013 አንቀፅ 2(1) መሠረት ጠበቃ ማለት የግል የጥብቅና አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ የተሰጠው ሰው ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 8 ላይ ለተደነገገው በውጭ ሀገር ሕግ መሠረት የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ የተሰጠውን ሰውም ያካትታል፡፡ በተመሳሳይ የጥብቅና ድርጅት ማለት ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆኑ የፀና የጥብቅና ፈቃድ ባላቸው ጠበቆች የጥብቅና አገልግሎት ለመስጠት ማቋቋም ድርጅት ነው፡፡

በተጨማሪም የጥብቅና ሙያ አገልግሎት ማለት የገንዘብ ክፍያ በመቀበል ወይም ወደፊት የሚገኝ ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ወይም ያለ ክፍያ በጠበቃ ወይም በጥብቅና ድርጅት የሚሰጥ ማንኛውም የህግ አገልግሎት ሲሆን በህግ ጉዳዮች ምክር መስጠት፣ ከወንጀል ጉዳዮች ወጪ የማደራደር ሥራ መስራት፣ የህግ ሰነድ ማዘጋጀት ወይም በደንበኛ ስም ሰነድ ማቅረብ፣ በፍርድ ቤት፣ በአስተዳደራዊ ጉባኤዎች፣ ከፊል የዳኝነት ስልጣን ባላቸው አካላት፣ በግልግል ዳኝነት ጉባኤዎች እና በሌሎች አማራጭ የሙግት መፍቻ መድረኮች ደንበኛን ወክሎ መቅረብና መከራከርን እንደሚያጠቃልል በአዋጁ አንቀፅ 2(5) መረዳት ይቻላል፡፡

የጥብቅና ፈቃድ አይነቶችና ፈቃድ ለማግኘት ሊሟሉ የሚገባቸው መስፈርቶች
በአዋጁ አንቀፅ 11 መሰረት ሶስት ዓይነት የጥብቅና ፍቃዶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጥብቅና ፍቃድ ሲሆን ይህም በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሥልጣን ሥር ለሚታዩ ጉዳዮች የጥብቅና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው፡፡ ሁለተኛው የፌደራል ማናቸውም ፍርድ ቤት የጥብቅና ፍቃድ ሲሆን ይህም ከፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚታዩ ጉዳዮች የጥብቅና ፈቃድ መስጠት የሚያስችል ነው፡፡ ሶስተኛው የፌደራል ልዩ ጥብቅና ፍቃድ ሲሆን ለህብረተሰቡ አጠቃላይ መብት እና ጥቅም መከበር በነፃ አገልግሎት ለሚሰጥ ሰው ወይም ድርጅት እንዲሁም አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የህግ ድጋፍ አገልግሎት ለሚሰጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ህግ ትምህርት ቤቶች እና የህግ መምህራን የሚሰጥ ፈቃድ ነው፡፡

እነዚህ ፈቃዶች እያንዳንዳቸው እንደየባህሪያቸው የሚጠይቋቸው ተጨማሪ መስፈርቶች ቢኖሩም የትኛውንም የጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ ለማግኘት በመሰረታዊነት መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች በአዋጁ አንቀፅ 6 ተመልክተዋል፡፡ እንዚህም
 የኢትዮጵያ ዜግነት ያለው ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊ መሆን
 እውቅና ካለው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቢያንስ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው መሆን
 ለመጨረሻ ጊዜ ይሰራበት ከነበረበት ተቋም ድርጅቱን ከመልቀቁ በፊት ባሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በከባድ ዲስፕሊን ጥፋት ያልተቀጣ እና የመልካም ሥነ-ምግባር ማረጋገጫ ማቅረብ መቻል
 በሕግ ሙያ የሚፈለገውን የሥራ ልምድ ያሟላ መሆን እና
 እንደ አስፈላጊነቱ ፍቃድ ለማግኘት የሚሰጠውን የሙያ መግቢያ ፈተና ያለፈ መሆን ናቸው፡፡
እንዚህን መስፈርቶች የማያሟላ ሰው የጥብቅና ፈቃድ ሊሰጠው አይችልም፡፡ በተጨማሪም ታስቦበት በሚፈፀምና ከሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት ጋር በተያያዘ 3 አመትና ከዚያ በላይ ፅኑ እስራት በሚያስቀጣ ወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ የተባለና አግባብነት ባለው ህግ ያልተሰየመ ወይም በህግ አገልግሎት እንዳይሰማራ በህግ ወይም በፍርድ ቤት የከተከለከለ ሰው የጥብቅና ፈቃድ ሊሰጠው እንደማይችል በአዋጁ አንቀፅ 7 ተደንግጓል፡፡

የጠበቆች ሙያዊ ግዴታዎች 

ጠበቃዎች በአዋጁ የተመለከቱ የጠበቆች የሙያ ግዴታን ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህም ግዴታዎች በአዋጁ ከአንቀጽ 22 እስከ 24 እንዲሁም በአንቀፅ 26 እና 31 የተደነገጉ ሲሆን ማንኛውም ጠበቃ ወይም የጥብቅና ድርጅት፡-
በደንበኛው፣ በፍርድ ቤት ወይም በማንኛውም አግባብ ባለው አካል የጥብቅና ፍቃድ እንዲያሳይ ሲጠየቅ የማሳየት ግዴታ አለበት፡፡ በተመሳሳይ አንድ ጠበቃ የጥብቅና ፍቃዱን በማንኛውም ሁኔታ ለሌላ ሰው መጠቀሚያ ወይም መገልገያ አሳልፎ መስጠት የለበትም፡፡
ለአጭር ጊዜ ከሚሰጥ የህግ ምክር አገልግሎት ውጪ ከደንበኛው ጋር የሚያደርገውን የጥብቅና አገልግሎት ውል በጽሑፍ ማድረግ አለበት፡፡ ውሉ ደንበኛው ለጠበቃው የሚከፍለውን አጠቃላይ የገንዘብ ክፍያ፣ የአከፋፈሉን ስልት እና ጊዜ፣ ጠበቃው በጉዳዩ ላይ የሚሰጠውን የጥብቅና አገልግሎት የሚያካትት መሆን አለበት፡፡
ለጥብቅና አገልግሎት መስጫ የሚሆን ቢሮ የማሟላት፣ የጥብቅና ሥራን በአገናኝ አማካኝነት ያለመስራት፣ የጥብቅና ውልን ያለበቂና ሕጋዊ ምክንያት ያለማቋረጥ እና በጥብቅና ውሉ ከተገለፀው የክፍያ መጠን በላይ ተጨማሪ ክፍያ ከደንበኛ ያለመጠየቅ ግዴታ አለበት፡፡
የአገልግሎት ሥራውን በታማኝነት መስራትና የፍትህ አጋር መሆን አለበት፡፡
ያለበቂ ምክንያት ጉዳይን ያለማጓተት፣ ምስክሮችን በሀሰት ያለማደራጀት፣ ሀሰተኛ ማስረጃ ያለማቅረብ ወይም ያለማስቀረብ፣ ተዘጋጅቶ የመቅረብና ተገቢውን ክርክር የማድረግ፣ የሕግ መሠረት የሌለውንና የማያዋጣ ጉዳይን ያለመያዝ፣ የደንበኛውን ወይም ባለጉዳዩን ምስጢር ያለማውጣት እና ሌሎች መሰል የሥነ-ምግባር ግዴታ አለበት፡፡
እንደጉዳዩ ክብደትና ቅለት እየታየ በዓመት ከሶስት ጉዳይ ያልበለጠ ነፃ የጥብቅና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ አገልግሎቱ የሚሰጠውም የመክፈል አቅም ለሌላቸው ሰዎች፣ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ለሲቪክ ማኅበራት እና ለማኅበረሰብ ተቋማት፣ ፍርድ ቤት የጥብቅና አገልግሎት እንዲያገኙ ለሚጠይቅላቸው ሰዎች፣ ሕግን፣ የሕግ ሙያን እና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ለሚሰሩ ኮሚቴዎች እና ድርጅቶች ነው፡፡
በዓመት ውስጥ በድምሩ ከ24 እስከ 30 ሰዓት የሚደርስ የሕግ ሥልጠና የመውሰድ ግዴታ አለበት፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ኃላፊነት ያልተወጣ ጠበቃ ወይም የጥብቅና ድርጅት እንደ ነገሩ ሁኔታ በአዋጁ አንቀጽ 84 እና 85 በቀላል እና በከባድ የዲስፕሊን ጥፋት ይቀጣል፡፡ ይህ ቅጣት የፍትሐብሔርና የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስቀር አይደለም፡፡

ማጠቃለያ
በአጠቃላይ ጠበቆች ለፍትህ መስፈን የማይተካ ሚና ያላቸው በመሆኑ የሙያ ሥነ ምግባርን በማክበር ሀላፊነታቸውን ሊወጡ የሚገባ ሲሆን ህብረተሰቡም ለህጉ መከበር አስተዋፅኦ ከማድረግ በተጨማሪ በህግ መሰረት ግዴታቸውን በማይወጡት ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍን የበኩሉን ሊያበረክት ይገባል፡፡
በንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ
ፍትህ ሚኒስቴር
Stay Connected with #AleHig
https://linktr.ee/alehig

LegalAwareness #AleHig #LegalUpdates #AccessToJustice

Comments are closed

Compare Listings

Title Price Status Type Area Purpose Bedrooms Bathrooms