AleHig Law Office is a premier legal office specializing in a wide range of legal services in Ethiopia, Addis Ababa, including government engagement, corporate law, investment, commercial law, business law, property disputes, family law, succession, and civil law cases

FOLLOW US ON:

Get in touch!

Addis Ababa, Ethiopia

የአመክሮ አፈፃጸም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ

  • Home
  • Legal Update
  • የአመክሮ አፈፃጸም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ

የአንድ አገር የወንጀል ፍትህ ስርዓት ውጤታማ እንዲሆን ከሚያስችሉት ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው በወንጀል ህጉ የተቀመጡትን ዝርዝር ቅጣቶች በአግባቡና በተሟላ ሁኔታ ማስፈጸም መቻል ነው። የወንጀል ጥፋተኝነትን ተከትሎ ልዩ ልዩ የቅጣት እርምጃዎች ተግባራዊ የሚደረጉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ እንደየ ሀገራቱ የወንጀል ፖሊሲ የእስር ቅጣት፣ የገንዘብ መቀጮ፣ የግዴታ ስራ፣ እና ሌሎች ክልከላዎች ጥፋተኛው ላይ ሊጣሉ ይችላሉ።

ይህ ሁኔታ ቢኖረም በአንዳንደ ልዩ ሁኔታዎች ደግሞ በወንጀል ክስ ጥፋተኛ የተባለ ሰው ነፃነትን በሚያሳጣ እስር ቅጣት ተቀጥቶ በማረሚያ ቤት የሚገኝ ሆኖ ነገር ግን በማረሚያ ቤት ከሚቆይ ይልቅ ወደ ማህበረሰቡ ቢቀላቀል ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ሲታሰብ የተፈረደበትን የእስር ጊዜ በተወሰነ መጠን ከጨረሰ በኋላ ከእስር ተለቆ በሙከራ ጊዜ ቅጣቱን በውጭ እንዲጨርስ ይደረጋል። በአገራችን ከእነዚህ የእስር ውጭ ያሉ ዋናዋና አማራጮች ውስጥ እንደ ይቅርታ፣ ምህረት፣ አመክሮና የቅጣት ገደብ የመሳሰሉት በህግ እውቅና ተሰጥቷቸው እናገኛለን።

በወንጀል ፍርደኛ አያያዝ ሂደት ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ማረሚያ ቤቶች ሲሆኑ ታራሚዎችን ከመጠበቅ ባሻገር ለጠቅላላ ሰብዕናቸው ግንባታ የሚያስፈልጋቸውን ትምህርት፣ ልዩ ልዩ የሙያ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ፡፡ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት በሚያከናውኗቸው ተግባራት የታራሚዎችን ባሕርይ በማሻሻል በየጊዜው የሚገመግሙ ሲሆን ይህንን የባሕርይ ለውጥ ማሳየት የቻሉ ታራሚዎችን ሙሉ የእሥራት ጊዜያቸውን መፈጸም ሳይጠበቅባቸው ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ ለማድረግ አመክሮን በመስጠት ሂደት የራሳቸው ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። በዚህ አጭር ጽሁፍ ውስጥ በተለይም ስለ አመክሮ ምንነት፣ ህጋዊ ማዕቀፍ፣ የአፈፃጸም ሂደት፣ የአመክሮ ተጠቃሚ ለመሆን መሟላት ስለሚገባቸው ዝርዝር ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሁም የአመክሮ ውሳኔ ቀሪ ስለሚሆንባቸው ሁኔታዎች ለማብራራት ተሞክሯል።

የአመክሮ ምንነት
እንደሜሪያም ዌብስተር የህግ መዝገበ ቃላት (Webster’s Law dictionary) ከሆነ Parole means a conditional release of a prisoner who has served part of a sentence and who remains under the control of and in the legal custody of a parole authority” ወይም” አመክሮ ማለት አንድ ታራሚ የእሥራት ጊዜውን ሙሉ በሙሉ ከመፈጸሙ በፊት በገደብ ወይም በሁኔታ ላይ ተመስርቶ ከእስር የሚለቀቅበትና ገደቡን ተላልፎ ሲገኝ እንደ አስፈላጊነቱ ወደነበረበት ማረሚያ ቤት እንዲመለስ የሚደረግበት አሠራር ነው” ሲል ትርጉም ይሰጠዋል። በዚህ ትርጉም መሰረት ለአመክሮ ጽንሰ-ሐሳብ ዋነኛው ጉዳይ በወንጀል ጥፋት የእስር ቅጣት ተላልፎበት በማረሚያ ቤት የሚገኝ ታራሚ መኖርና ይህንኑ የእስር ዘመን አለመጨረስ የሚሉ ነጥቦችን እንደቁልፍ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠ መሆኑን ነው።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አመክሮን በተመለከተ ከአንቀጽ 201 እስከ አንቀጽ 207 ባሉ ድንጋጌዎች መሠረታዊ መርሆዎችን አካቷል። ይሁን እንጂ ከላይ በተመለከትነው አግባብ የጽንሰ ሃሳቡን ምንነት አስመልክቶ ግልጽ ትርጉም አልሰጠም።

በአመክሮ ለመለቀቅ መሟላት ያለባቸው ቅድመ-ሁኔታዎች
በአመክሮ የሚለቀቀው ታራሚ ከላይ እንደተመለከተው መልካም ዝርዝር ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ያለበት ሲሆን እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎችንም ህጉ ከአንቀጽ 201-204 ድረስ በዝርዝር ደንግጓል፡፡ እነዚህም፣
1ኛ፣ በፍርድ ቤት ከተላለፈው ቅጣት 2/3ኛውን መፈጸም፣ የእድሜ ልክ እስራት በሚሆንበት ጊዜ ቢያንስ 20 ዓመት እስር ሲፈጽም፣
2ኛ፣ ከተበዳይ ጋር በተደረገ ስምምነት (እርቅ) ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት ሊከፍል የሚገባውን ካሳ መክፈል፣
3ኛ፣ በማረሚያ ቤት ቆይታው በሥራውና በጠባዩ መሻሻል ማሳየትና
4ኛ፣ ተቀጪው “ልማደኛ ደጋጋሚ” አለመሆን ናቸው፡፡
እነዚህ መስፈርቶች ከተሟሉና ታራሚው ቢለቀቅ ከማህበረሰቡ ጋር በመልካም ሁኔታ ሊኖር የሚያስችለው መልካም ጠባይ አለው ተብሎ ከታመነበት በአመክሮ ሊለቀቅ ይችላል፡፡ ሆኖም በአመክሮ መለቀቅ ሙሉ በሙሉ ነጻነትን የሚያጎናጽፍ ሳይሆን ይልቁንም የቀረውን 1/3ኛ ቅጣት ታራሚው በገደብ ወይም ሥልጣን በተሰጠው አካል ክትትል ሥር ሆኖ እንዲፈጽም የሚደረግበት የቅጣት አፈጻጸም ሥርዓት ነው፡፡ የዚህን ቅጣት አፈጻጸም ሥርዓት የበለጠ ፍሬያማ ለማድረግ የአመክሮ ተጠቃሚው በተጨማሪ የፈተና ጊዜ እንዲቆይ የሚደረግበትን አሰራር ለማበጀት ለፍርድ ቤቶች የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት አመክሮን የሚወስነው ፍርድ ቤት የአመክሮ ተጠቃሚው በፈተና ጊዜ እንዲቆይ ለመወሰን አንዳንድ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ይወስናል፡፡ የፈተና ጊዜውም በማንኛውም ሁኔታ ከሁለት ዓመት ሊያንስ ከአምስት ዓመት ሊበልጥ እንደማይችል ሕጉ ይደነግጋል፡፡ ሆኖም በአመክሮ የሚለቀቀው ሰው የእድሜ ልክ እስረኛ በሆነ ጊዜ ፈተናው ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ጊዜ እንዲሆን በልዩ ሁኔታ ሊወሰን ይችላል፡፡ እንዲህ አይነቱ ልዩ ውሳኔ በፍርድ ቤት በአመክሮ ጊዜ ካልተሰጠ የፈተና ጊዜው በፍርድ የተመለከተው የቅጣት ዘመን ሲጠናቀቅ የፈተና ጊዜው አብሮ እንደተጠናቀቀ የሕግ ግምት መውሰድ ይቻላል።

ከዚህ ውጭ፣ ተቀጪው ጥፋተኛ ልማደኛ ደጋጋሚ ከሆነ ማለትም በተለያየ ጊዜ በወንጀል ድርጊት ተሳትፎ የሚታወቅ (Recidivist) ከሆነ፣ ታራሚውን የሚያስተዳድረው ማረሚያ ቤት ለአመክሮ የሚያበቃ የባህሪ ለውጥ አላመጣም ብሎ ያመነ እንደሆነ፣ ከተጎጂ ቤተሰብ ጋር እርቅ ለመፈጸም ያልቻለ እንደሆነና ተገቢ ካሳ ሳይከፍል ከቀረ ምንም እንኳ የቅጣት ውሳኔውን 2/3ኛ ቢፈጽምም የአመክሮ ተጠቃሚ እንደማይሆን ከድንጋጌዎቹ መረዳት ይቻላል።

ዝርዝር የአመክሮ አፈፃጸምና የታራሚዎች መብት፣
ታራሚዎች ያሳዩትን የባሕርይ ለውጥ መሠረት በማድረግ የሚሰጠው አመክሮ አፈፃጸሙ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግና እሱን ለማስፈጸም በወጣ መመሪያ መሠረት ይመራል፡፡ በዚህም መሰረት ማረሚያ ቤቶች ፍርደኛው በሚገባበት ጊዜ የተፈጸመበትን የቅጣት ጊዜ ከመጨረሱ በፊት በአመክሮ ሊወጣ እንደሚችል፣ በአመክሮ ለመውጣት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በዝርዝር ለታራሚው ማስረዳት ይጠበቅባቸዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ህጉ የጠባይ አመራር የቁጥጥር ደንብ እንደሚወጣ አስቀምጧል።

ተግባራዊ ሂደቱን በሚመለከት ታራው ለአመክሮ የሚያበቁ ሁኔታዎች የተሟሉ በመሰለው ጊዜ ልለቀቅ ብሎ አቤቱታ ሲያቀርብ ወይንም አግባብ ያለው አካል (የሚያስተዳድረው ማረሚያ ቤት) እስረኛው በአመክሮ እንዲለቀቅ ሀሳብ ሲያቀርብ አስተያየቱን ለፍርድ ቤት ያስተላልፋል። ፍርድ ቤቱም የቀረበለትን ሰነድ መርምሮ እስረኛው በአመክሮ እንዲለቀቅ ትዕዛዘዝ ሲሰጥ የፈተናውን ጊዜ ከላይ ከተገለጸው የጊዜ ገደብ ሳይበልጥ ማመልከት አለበት።

የአመክሮ ውሳኔ ውጤትና ቀሪ የሚሆንባቸው ምክንያቶች በውጤት ደረጃ አመክሮ ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት መስፈርቶች መነሻነት የሚሰጥ በእስር ላይ የሚገኙ ታራሚዎች መብት ቢሆንም ቀሪ የሚያደርገው የወንጀል ቅጣቱን እንጂ ወንጀለኝነትነ (Criminal Record) ሙሉ በሙሉ አያጠፋም። ይህም ማለት ወንጀለኛው አግባብነት ባለው የመሰየም ሂደት አልፎ ስሙን ከወንጀለኛነት መዝገብ እስካላስፋቀ ድረስ የወንጀለኝነት ታሪኩ የሚቀጥል ይሆናል። አንቀጽ 206(3) ይመለከቷል፣ ከዚህ በተጨማሪ አንድ ጊዜ በፍርድ ቤት የሚሰጥ የአመክሮ ውሳኔ በገደብ ላይ የተመሰረተ (Conditional Order) እስከሆነ ድረስ በገደቡ የተመለከቱት ግዴታዎች ባይማሉ ወይንም በተሰጠው የፈተና ጊዜ ውስጥ ሌላ ወንጀል ፈጽሞ ቢገኝ ውሳኔው ሊሻር ይችላል። የዚህም ውሳኔ መሻር ውጤት በህጉ አንቀጽ 206 (2) እንደተመላከተው ተለቆ የነበረው ጥፋተኛ ተመልሶ ወደ ነበረበት ማረሚያ ቤት እንዲገባ ይደረጋል። ከዚህ ባለፈም በአመክሮ ተፈቶ ያሳለፈው ጊዜ ቅጣቱ ላይ ሳይታሰብ ቀሪ ቅጣቱን በሙሉ እንዲፈጽም ይደረጋል። እንዲሁም በተባለው ጊዜ ውስጥ ሌላ ወንጀል ሰርቶ የተገኘ እንደሆነ ደጋጋሚነትን የሚመለከቱት የህጉ ክፍሎች ተፈፃሚ ይሆኑበታል።

ማጠቃለያ
አመክሮ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የታራሚዎችን የባሕርይ ለውጥ መሠረት አድርጎ የሚሰጥና ታራሚዎች ከእስር ተለቀው ወደ ማህበረሰቡ ተመልሰው ቀሪውን የቅጣት ጊዜ በሙከራ የሚያሳልፉበት ሁኔታ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ ስርዓት ውስጥ ከአመክሮ በተጨማሪ እስረኛ ከማረሚያ ውጭ ሆኖ ቅጣቱን እንዲጨርስ የሚደረግባቸው ሌሎች አሰራሮች መኖራቸውን በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ ለመጠቆም ተሞክሯል። በዚህም አመክሮ ከነዚህ አሰራሮች የሚለየው በፍርድ ቤት የሚሰጥ መብት መሆኑ ነው። በተጨማሪም ይህ በአመክሮ የመለቀቅ መብት ፍጹም አለመሆኑና በዚህ ጽሁፍ የተዘረዘሩት አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ብቻ የሚፈጸም መብት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

በንቃተ ህግ፣ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት

ፍትህ ሚኒስቴር ሚኪያስ መላክ +251920666595
አማራጭ የሕግ እውቀት አለ
Alternative legal enlightenment/ALE
Telegram
https://t.me/AleHig

Telegram_Group
https://t.me/AleHig_Group

Instagram
https://www.instagram.com/alehigofficial

YouTube
https://www.youtube.com/@Ale_Hig

LinkedIn
https://www.linkedin.com/company/alehig/

official website
https://www.alehig.com

Email address
Alehig7@gmail.com

Telegram Bot
@LawsocietiesBot

Comments are closed

Compare Listings

Title Price Status Type Area Purpose Bedrooms Bathrooms